የ82 ዓመቷ አያት ባደረጉት ንቅናቄ በአረጋውያን መኖሪያ ውስጥ መጠጥ የሚፈቅድ ሕግ ወጣ

የፎቶው ባለመብት, LeBrun Family
የ82 ዓመቷ አኒታ ለቡርን አምስት የልጅ ልጆች አሏቸው። ከሰዓት 11 ሰዓት አካባቢ ወይን መጠጣት ያዘወትራሉ።
አምና በአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት የሚገኘው የአረጋውያን የጋራ መኖሪያ አልኮል መጠጥ መከልከሉን ሲሰሙ ለማመን ተቸግረዋል።
አሚራ ቾይስ ቻምፒዮን በተባለው የአረጋውያን የጋራ መኖሪያ ውስጥ ከሚገኙ የዕድሜ ባለ ጸጎች ጋር በቀላሉ የተግባቡት አኒታ በውሳኔው አልተደሰቱም።
የአረጋውያን የጋራ መኖሪያው ያወጣውን ሕግ እንዲቀለብስ ንቅናቄ ጀመሩ። የከተማው ምክር ቤት ከአንዴም ሁለቴ ቀርበው ቃላቸውን ሰጥተዋል።
በዚህም መጠጥ ላይ ተጥሎ የነበረው ክልከላ የተነሳ ሲሆን፤ አዲስ የወጣው ድንጋጌ 'ግራንድፓረንትስ ሀፒ አወር' ተብሏል። አያቶች በነጻነት መጠጥ የሚጎነጩበት ሰዓት እንደማለት ነው።
ሕጉ ከዚህ ወር ጀምሮ ይተገበራል። በሜኔሶታ ግዛት የሚገኙ የአረጋውያን የጋራ መኖሪያዎች አልኮል መጠጥ እንዲያቀርቡም ይፈቅዳል።
በማቆያዎቹ ለሚኖሩ አዛውንቶች እንዲሁም ለእንግዶች ልዩ መርሃ ግብር ሲኖር ያለ ፈቃድ መጠጥ ማቅረብ ይቻላል።
ነገር ግን አስቀድሞ ለከተማ መስተዳድሩ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

የፎቶው ባለመብት, Amira Choice and Ebenezer Senior Living
ውሳኔውን ተከትሎ አኒታ "በጣም ነው የኮራሁት። ብዙ ሰዎች ደስ ብሏቸዋል" ብለዋል።
አብረዋቸው በአዛውንት ማቆያው የሚኖሩ አረጋውያን መጠጥ ላይ ተጥሎ የነበረውን ክልከላ "ረብ የለሽ" እንደሆነ ይናገሩ እንደነበር ጠቅሰዋል።
በአሜሪካ በአረጋውያን የጋራ መኖሪያዎች ወይም አዛውንቶች ድጋፍ እየተሰጣቸው በሚኖሩባቸው ተቋማት ውስጥ ያለው የመጠጥ አቅርቦት ውሳኔ ከግዛት ግዛት ይለያያል።
አብዛኞቹ ተቋማት አዛውንቶች በመርሃ ግብሮች ላይ መጠጥ እንዲጠጡ እና ማኅበራዊ ትስስራቸውን እንዲያጠናክሩ ያበረታታሉ።
አኒታ የሚኖሩበት ተቋም ሠራተኛ የሆነችው ሳራ ሉህማን እንደምትለው አዛውንቶች በክፍላቸው ውስጥ ሆነው መጠጣት ወይም በማኅበራዊ መሰናዶዎች መጠጥ መውሰድ ይችላሉ።
አረጋውያን እንዳይወድቁ በሚል ከሁለት ብርጭቆ በላይ እንዲጠጡ ይከለከላል።
አገረ ገዢው ቲም ዋልዝ ሕጉ ጸድቆ የፊርማ ሥነ ሥርዓት ሲደረግ "ማርጀት የሚያስደስቱንን ልማዶች እና ነጻነትታችንን ሊቀማን አይገባም" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Handout
አገረ ገዢው እንዳሉት፤ ሕጉ መጽደቁ የአረጋውያን የጋራ መኖሪያዎች አዛውንቶች ልደት፣ ዓመታዊ በዓል እና ሌሎችም የመዝናኛ ማኅበራዊ ክንውኖች ላይ መጠጥ እንዲጠጡ ለማስፈቀድ የሚያልፉትን ሒደት ያስቀራል።
አኒራ ሕጉ እንዲለወጥ ንቅናቄ ማድረግ የጀመሩት በአውሮፓውያኑ 2025 በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ሻምፓኝ በመቅረቡ ከከተማው መስተዳድር ነቀፌታ መነሳቱን ተከትሎ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Amira Choice and Ebenezer Senior Living
አኒታ የሚኖሩበት ተቋም 'ሊዲንግኤጅ ሚኔሶታ' ከተባለ ለአዛውንቶች ተንከባካቢዎች ድጋፍ የሚሰጥ ተቋም እርዳታ ጠይቋል።
በሊዲንግኤጅ ሚኔሶታ የምትሠራው ኤሪን ኸፐርት እንደምትለው፤ አዛውንቶች የሚኖሩበት ተቋም "ቤታቸው" ስለሆነ "በሕጋዊ መንገድ አልኮል መጠጣት" ሊፈቀድላቸው ይገባል።
"ቤታቸው ቢሆኑ እንደሚያደርጉት ሁሉ በሚኖሩበት ተቋምም" ፈቃድ ሊያገኙ እንደሚገባ ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም በኮንከት የአዛውንቶች መንከባከቢያ ተቋም የ96 ዓመት የቲክቶክ ኮከብ የሆኑት ሊሊያን ድሮኒክ መጠጥ መከልከሉን በተመለከተ ቅሬታ አሰምተው ነበር።
15.1 ሚሊዮን ተከታዮች ያሏቸው ሊሊያን ድግስ ላይ መጠጥ እንዳያቀርቡ መከልከላቸውን ተችተዋል።
የልጅ ልጃቸው ኬቨን ዶሪክ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ ሊሊያን የሜኔሶታውን መጠጥ የሚፈቅድ ሕግ ሲሰሙ በጣም ተደስተዋል።
"ተዋቸው ይጠጡ!" ሲሉም ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
የአኒታ መኖሪያ በቀጣይ ወር ለአዛውንቶች ድግስ አሰናድቷል።
አኒታንም "ሕግ ያስለወጠችው ኮከብ" ሲሉ ነዋሪዎች አሞካሽተዋል።
በሜኔሶታ ሁለቱም ምክር ቤቶች ቃላቸውን ሲሰጡ "ስላረጀን እና በድጋፍ መስጫ ተቋም ስለምንኖር ነጻነታችን ከሌሎች ሰዎች ያነሰ ሊሆን አይገባም " ብለዋል።
"እኔ እና ጓደኞቹ በነጻነት መጠጥ የምንጠጣበትን ሰዓት እንወደዋለን። እናንተም ትወዱታላችሁ። አብረን እየጠጣን የድሮው ሕይወታችንን እናስታውሳለን። ስለሰጠነው ወታደራዊ አገልግሎት፣ ቤተሰብ ስለመመሥረት፣ ጓደኞችን ስለማጣት እና በወርቃማው ዘመናችን ስለመኖር እናወጋለን።"















