ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማሕጸን ኪራይ ልጅ ያገኙት ጀርመናዊ ፖለቲከኛ በፓርቲያቸው በመተቸታቸው ከኃላፊነት ለቀቁ
የጀርመን መሀከለኛ-ቀኝ ዘመም ፖለቲከኛ ጀንስ ስፓሀን በማሕጸን ኪራይ ልጅ ከማግኘታቸው ጋር በተያያዘ የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ።
በጀርመን የሴቶችን ማሕጸን ተከራይቶ ልጅ ማስወለድ (Surrogacy) ክልክል ሲሆን፤ ፖለቲከኛው በማሕጸን ኪራይ ልጅ ያገኙት በአሜሪካ ነው።
ጀርመንን የሚመራው ጥምር ፓርቲ አካል የሆነው 'ክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ' የማሕጸን ኪራይ ላይ የተጣለውን ክልከላ ይደግፋል።
ጀንስ የዚህ ፓርቲ አባል ሆነው ሳለ በማሕጸን ኪራይ ልጅ ማግኘታቸው "ግብዝነት ነው" በሚል ተተችተዋል።
በእርግጥ ከጀርመን ውጭ በማሕጸን ኪራይ የተወለዱ ልጆችን ማሳደግን ሕጉ አይከለክልም።
ሆኖም ግን በጀመርን ምክር ቤት የፓርቲያቸው ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ያገለግሉ የነበሩት ፖለቲከኛው ከኃላፊነታቸው ለቅቀዋል።
ፖለቲከኛው ትናንት ቅዳሜ ባወጡት መግለጫ "የግል ደስታዬ እንዲሁም ከባለቤቴ ጋር ቤተሰብ መሥርቼ አባት መሆኔ ከፖለቲካ ኃላፊነቴ ጋር አብሮ እንደማይሄድ ተረድቻለሁ" ብለዋል።
የጀርመን መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ መርዝ ውሳኔውን "ትክክለኛ" እና "አይቀሬ" ብለውታል።
በፖለቲከኛው ምትክ ሌላ ኃላፊ እንደሚሾሙ ጠቅሰው "ታማኝነት ትልቁ የፖለቲካ ሃብት ነው" ብለዋል።
የ46 ዓመቱ ፖለቲከኛ የጤና ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን ከባላቸው ዳንኤል ፉንኬ ጋር በማሕጸን ኪራይ ወላጆች ለመሆን መብቃታቸውን የገለጹት ባለፈው ሳምንት ነበር።
በዚህም ፓርቲያቸውን ጨምሮ ከሌሎችም ፓርቲዎች ትችት ቀርቦባቸዋል።
ጀንስ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን በገለጹበት ጽሑፍ "በማሕጸን ኪራይ ወላጅ የመሆን የግል ውሳኔዬን እና በምክር ቤት የፓርቲዬ ኃላፊ መሆኔን ለማማጣም ያደረግኩት ጥረት ከገመትኩት በላይ ከባድ ሆኖብኛል" ብለዋል።
የማኅበረሰቡ "የማያቋርጥ ውይይት" ቆም ብለው ውሳኔያቸውን "እንዲያጤኑ" እንዳደረጋቸው ጠቅሰዋል።
"በዚህ ጉዳይ ላይ ግልጽ እና ጠንካራ አቋም ቢኖረንም ሁሌም ሰብአዊ በሆነ መንገድ መጋገር አለብን" ብለዋል።
ተተኪ እስከሚገኝ ድረስ የክርስቲያን ሶሻል ዩኒየን ኃላፊ አሌክሳንደር ሆፍማን ሥልጣኑን እንደሚረከቡ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ክርስቲያን ዲሞክራት ፓርቲ የማሕጸን ኪራይ ክልከላን በጽኑ ሲደግፍ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 2020 የጤና ሚኒስትር የነበሩት ጀንስ ክልከላው እንዲላላ በሊበራሉ ኤፍዲፒ የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።
በ2015 "እንደ ተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ክርስቲያንነቴ የማሕጸን ኪራይን ለመደገፍ ይከብደኛል" ብለዋል።
የማሕጸን ኪራይ በጀርመን እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት እና በገንዘብ ያስቀጣል።
ስለዚህም ጀርመናዊያን ጥንዶች በውጭ አገራት በማሕጸን ኪራይ ልጅ ያገኛሉ።
ጀንስ ስፓሀን በጀርመን ተሰሚነት ካላቸው ፖለቲከኞች አንዱ ናቸው። ከዚህ ቀደም ሌሎች ቅሌቶችን ማለፍ ችለዋል።
ከማሕጸን ኪራይ ጋር ትችት የቀረበባቸው ፓርቲያቸው የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት በተቸገረበት ወቅት ነው።
ውዝግቡ በቀጣይ በሚካሄደው ቁልፍ ምርጫ የሚጎዳቸው ይሆናል።በምርጫው ቀኝ አክራሪዎች አብላጫ ድምጽ ሊያገኙ ይችላሉ።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ቀኝ አክራሪዎች ሥልጣን ሲይዙ የመጀመሪያው ይሆናል።
ጋዜጠኛ ክርስቲያን ዎልፈል "ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ፖለቲከኛ ልጅ የሌላቸው ጀርመናዊያን ጥንዶችን መብት ነጥቀዋል" ብለዋል።
የጀመርን መራሔ መንግሥት በፖለቲከኛው ከኃላፊነት መልቀቅ ደስተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይታመናል።
እንደ ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ጣሊያን ያሉ ሌሎችም የአውሮፓ ኅብረት አገራት የማሕጸን ኪራይን አይፈቅዱም።