ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጦርነት ወቅት ኢኮኖሚ ያዳከማቸው ሩሲያውያን በጥሬ ገንዘብ መገበያየትን እየመረጡ ነው
በሩሲያ የሞባይል ኢንተርኔት መዘጋት በካርድ የሚፈጸሙ ክፍያዎችን በማስተጓጎሉ እንዲሁም የንግድ ባለቤቶች ግብር ክፍያን ለማምለጥ በመፈለጋቸው የአገሪቱ ዜጎች በጥሬ ገንዘብ ወደሚደረግ የንግድ ልውውጥ እየተመለሱ ነው።
ከአራት ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከዩክሬን ጋር እየተዋጋች ባለችው ሩሲያ ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና ተፈጥሯል። የሩሲያ መንግሥት የአውሮፓውያኑ 2026 ከተጀመረ ወዲህ ብቻ 20 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የሩሲያ ሩብል ወደ ገበያው አስገብቷል።
የሩሲያ ማዕከላዊ ባንክ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዚህ ዓመት ወደ ገበያ የገባው የገንዘብ መጠን ከኮቪድ-19 ውጭ ወረርሽኝ በነበሩ ሌሎች ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ነው።
ይህ ጭማሪ የታየው ዩክሬን የምትፈጽማቸው የድሮን ጥቃቶች ባየሉበት ወቅት ነው። በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት የሩሲያ መንግሥት በሰፊው የአገሪቱ ክፍል የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎትን አቋርጧል።
ይህም በርካቶች በካርድ ክፍያ እንዳይፈጽሙ አድርጓቸዋል። መንግሥት እንደሚገልጸው ኢንተርኔት መቋረጡ የድሮን ጥቃቶቹን ለመመከት ያለመ ነው።
አንዲት የሞስኮ ከተማ ነዋሪ "ጥሬ ገንዘብ በእጅ መያዝ የተወሰነ የቁጥጥር እና የደኅንነት ስሜት ይሰጣል" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ከተማው ውስጥ ድንገተኛ ነገር አጋጥሞ የሞባይል ኔትወርክ ቢጠፋም መሠረታዊ ፍላጎቶቼን መግዛት እንደምችል አውቃለሁ" ስትል ገንዘብ በጥሬ መያዝን የምትመርጥበትም ምክንያት ገልጻለች።
ራሳቸውን ቁርጡ ካልታወቀ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚሞክሩት ሩሲያውያን ከዚህ ቀደም በጦርነቱ ወቅት በከፍተኛ መጠን ከባንክ ገንዘብ ያወጡባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።
በመስከረም 2022 ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከፊል ወታደራዊ ዘመቻ ባወጁበት እንዲሁም በሰኔ 2023 የዋግነር የቅጥር ወታደሮች ለአጭር ጊዜ ባመጹበት ወቅት የገንዘብ ዝውውር እጅግ ከፍ ብሎ ታይቷል።
ነዋሪዎች ጥሬ ገንዘብን መምረጣቸው፤ የመንግሥትን ታክስ የመሰብሰብ ሂደት አዳጋች አድርጎታል። የበጀት ጉድለቱ የሰፋበት አገሪቱ መንግሥት በአንጻሩ፤ ዩክሬን ውስጥ የሚያደርገው ጦርነት ለመደገፍ እያንዳንዷን ሩብል መሰብሰብ ይፈልጋል።
መንግሥት ገቢውን ለማሳደግ ካለፈው ጥር አንስቶ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ምጣኔውን ከነበረበት 20% ወደ 22% አሳድጓል። ቫት መከፈል የሚጀምርበትን የገቢ መጠን ዝቅ በማድረጉም አነስተኛ እና መካከለኛ የንግድ ተቋማት ግብሩን ከሚከፍሉት መከካል ሆነዋል።
በከፍተኛ ታክስ እና በተቀዛቀዘ ኢኮኖሚ ምክንያት የሚያገኙት ትርፍ የቀነሰባቸው ፋርማሲዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የውበት ሳሎኖች እና ሱቆች፤ ሽያጫቸውን ከመዝገብ ውጪ ለማድረግ ሲሉ ደንበኞቸቻውን በጥሬ ገንዘብ እያስከፈሉ ነው።
በሩሲያ ግዙፉ የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ማኅበር የሆነው 'ኦፖራ ሩሲያ' ግንቦት ላይ ያደረገው ጥናት እንደሚያሳየው፤ 6 በመቶ ገደማ ሥራ ፈጣሪዎች አዲሱን የታክስ ጫና ለመቋቋም ሲሉ እንደ የካሽ ሬጂስተር ደረሰኝ አለመስጠት ያሉ "ግራጫ አሠራሮች" መከተል ጀምረዋል።
በጥሬ ገንዘብ የሚፈጸም ክፍያ የንግድ ተቋማት ገቢያቸው ቫት መከፈል ከሚጀምርበት ጣሪያ በታች እንዲሆን ያደርጋቸዋል። በተጨማሪም የደመወዝ ግብርን ለመሸሽ ያግዛቸዋል።
የሩሲያ መንግሥት ይህንን ዓይነቱን በስውር የሚካሄድ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መቆጣጠርን ቀዳሚ ግቡ አድርጎታል። ፕሬዝዳንት ፑቲን የቫት ጭማሪው ተግባራዊ ከመሆኑ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሚወጡ አዲስ ሕጎች የንግድ ተቋማት ወደ ስውር አሠራሮች እንዳያደርጉ መሠራት እንዳለበት ተናግረው ነበር።
በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱ "ሕገ-ወጥ ቅጥርን እጅግ በከፍተኛ መጠን መቀነስ" እንደሚገባም ገልጸው ነበር።