ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ግብፅ እና ኤርትራ ቀይ ባሕርን "በሕገ ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚደረግ ሙከራን" አወገዙ
ግብፅ እና ኤርትራ የቀይ ባሕር "ደኅንነት እና አስተዳደር የሚመለከተው የጠረፉን አገራት ብቻ" እንደሆነ ገለጹ።
የጠረፉ አካል ያልሆኑ አገራት ቀይ ባሕርን "በሕገ ወጥ መንገድ ለመቆጣጠር የሚደረጉት ሙከራ ዓለም አቀፍ ሕግን የጣሰ ነው" ሲሉም አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።
የግብፁ ጋዜጣ አህራም ዛሬ እሁድ ሐምሌ 12/2018 ዓ. ም. በድረ ገጹ ባወጣው ዘገባ፤ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያደረጉትን ውይይት ተከትሎ የጋራ አቋማቸውን ይፋ ማድረጋቸው አስነብቧል።
የቀይ ባሕር ጠረፍ አካል ያልሆኑ አገራት "የደኅንነት [ጥበቃ] ሚናን ለመጫን" የሚያደርጉትን ሙከራ እንደሚያወግዙ ተገልጿል።
የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦስማን ሳልህ እና የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ በአገሮቻቸው መካከል ያለውን "ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስለ ማጠናከር" እንዲሁም በጋራ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋም እንዴት "ማስተባበር" እንዳለባቸው መምከራቸው ተገልጿል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ አገራቸው ኤርትራ "ሉዓላዊነቷን፣ ብሔራዊ ትስስሯን እና የግዛት አንድነቷን ለመጠበቅ" ለምታደርገው እንቅስቃሴ "ሙሉ ድጋፍ እንደምትሰጥ" አረጋግጠዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በቅርቡ በግብፅ ያደረጉት ጉብኝት "ፍሬያማ" እንደነበረ እና ለወደፊትም የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማሳደግ ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውም ተጠቅሷል።
ያለፈው ግንቦት ወር ላይ በቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የትራንስፖርት እንቅስቃሴን እና የወደብ ትስስርን የተመለከተ ስምምነት የተፈራረሙት ግብፅ እና ኤርትራ፤ የቀይ ባሕር ጉዳይ የሚመለከተው "የቀይ ባሕር ጠረፍ አገራትን ብቻ" እንደሆነ መግለጻቸው አይዘነጋም።
ሁለቱ አገራት፤ ቀይ ባሕር ከዳርቻው አገራት "ብሔራዊ ደኅንነት ጋር ቀጥተኛ ትስስር" እንዳለው በመጥቀስ "የቀይ ባሕር አጎራባች ያልሆነ አካል ቀይ ባሕርን በሚመለከቱ ጉዳዮች መግባት የለበትም" ማለታቸውም ይታወሳል።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በያዝነው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ግንቦት 30/2018 ዓ. ም. ወደ ግብፅ ተጉዘዋል።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የግብፅ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሌተናንት ጄነራል ከማል አልዋዚር፤ ግንቦት 8 ቀን 2018 ዓ. ም. ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር በአሥመራ መወያየታቸውም አይዘነጋም።
የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በዚህ ጉብኝት ወቅት የተፈረመው የባሕር ትራንስፖርት ትብብር ስምምነት እንዲተገበር ጥሪ ማቅረባቸውን የዛሬው የአህራም ዘገባ ይጠቁማል።
ሚኒስቴሩ ግብፅ የሁለትዮሽ ንግድን ለማሳደግ፣ የጋራ ኢንቨስትመንቶችን ለማበረታታት እና የካይሮ የግል ዘርፍ ኩባንያዎች በኤርትራ ገበያ ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ ለማስፋት ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።
ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች የማዕድን ቁፋሮ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ የባሕር ትራንስፖርት፣ የወደብ ትስስር፣ የመድኃኒት ምርት እና የዓሣ እርባታ መሆናቸው ተጠቅሷል።
የኤርትራ እና ግብፅ ሚኒስትሮች በሱዳን እና በሶማሊያ ያለውን ሁኔታ ጨምሮ ስለ አፍሪካ ቀንድ መወያየታቸውም ተገልጿል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብዲላቲ የአፍሪካ ቀንድን "የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት ቀጥተኛ ማራዘሚያ" ሲሉ ገልጸውት፤ ካይሮ የቀጣናውን "ደኅንነት እና መረጋጋት ለመጠበቅ" ቁርጠኛ መሆኗን መናገራቸው ተዘግቧል።
በተጨማሪም ብሔራዊ የመንግሥት ተቋማትን መደገፍ እንዲሁም የቀጣናው አገሮችን አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
ግብፅ "የመንግሥትን ሉዓላዊነት የሚጥሱ ወይም የቀጣናውን መረጋጋት የሚያውኩ ማንኛውንም ዓይነት የአንድ ወገን እርምጃዎች" እንደምትቃወም አክለዋል።
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ግብፅ እና ኤርትራ በቀይ ባሕር ጉዳይ እና በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች የፖለቲካ፣ የምጣኔ ሃብት እና ደኅንነት ትስስራቸውን አጠናክረዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ፍላጎቷን ይፋ ካደረገች በኋላ ግብፅ "ከበባ በሚመስል መልኩ" እየተንቀሳቀሰች ነው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነቢያት ጌታቸው መናገራቸው ይታወሳል።
ግንቦት 13/2018 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄዋን ካነሳች በኋላ ከግብፅ በኩል "ውጥረት፣ ትንኮሳ የሚመስሉ ነገሮች እየታዩ" መሆናቸውን ጠቁመዋል።