ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከ17 ወራት በኋላ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆን አሰናበተ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዙ ቶተንሃም ሆትስፐርስ ከ17 ወራት በኋላ አሰልጣኝ ጆዜ ሞሪንሆን ማሰናበቱን አስታወቀ።
ጆዜ ሞሪንሆ ከማንቸስተር ዩናይትድ ከተሰናበቱ በኋላ በለንደኑ ክለብ አንድ ዓመት ከአምስት ወራት ቆይተዋል።
ፖርቹጋላዊው ሞሪንሆ ቶተንሀምን ለማሰልጠን የተስማሙት በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2019 ላይ ማውሪሲዮ ፖቸቲኖን ተክተው ነው። ባለፈው ዓመት ቶተንሀም በሞሪንሆ እየተመራ ስድስተኛ ሆኖ ነበር የጨረሰው።
አሁን ቶተንሀም በፕሪምየር ሊጉ ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በማንቸስተር ዩናይትድ ሶስት ለአንድ ተሸንፎ ከኤቨርተን ደግሞ ሁለት አቻ ተለያይቷል። በተጨማሪም ባለፈው ወር ከአውሮፓ ሊግ በስላቪያ ፕራግ ተሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።
በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ ደግሞ በካራባዎ ካፕ ከማንቸስተር ሲቲ ይጫወታሉ። ሞሪንዮም በዚህ ጨዋታ ቡድኑንአይመሩም ማለት ነው።
ትናንት 12ቱ ክለቦች በአውሮፓ ሱፐር ሊግ ሊመሰርቱ መሆኑን ሲያስታውቁ ከሚሳተፉት የእንግሊዝ ክለቦች መካከል ቶተንሀም አንደኛው ነው።
የሆዜ ሞሪንሆ ረዳት አሰልጣኞች ጃዎ ሳክሪሜንቶ፣ ኑኖ ሳንቶስ፣ ካርሎስ ላሊን እና ጊዮቫኒ ሴራ አብረው መባረራቸውም ተገልጿል።
'' ሞሪንሆ እና ረዳቶቻቸው ቡድናችን ከባድ ጊዜያትን ሲያሳልፍ አብረውን ነበሩ'' ብለዋል የቶተንሀም ኃላፊ ደንኤል ሌቪ። ''ሞሪንሆ እውነተኛ ፕሮፌሽናል አሰልጣኝ ናቸው። በዚህ በወረርሽኙ ወቅት እንኳን ብዙ ነገሮችን ተቋቁመዋል''
'' በግል ደረጃ ከሞሪንሆ ጋር መስራት በጣም ያስደስተኛል። ሁለታችንም ባሰብነው መልኩ ነገሮች ባለመሳካታቸውና ይህ በመፈጠሩ አዝኛለሁ''
"ሁሌም ቢሆን ለሞሪንሆ በራችን ክፍት ነው። በዚህ አጋጣሚ አሰልጣኙ እና ረዳቶቻቸው ላደረጉት ነገሩ በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ።''
በዚህ የውድድር ዓመት ሆዜ ሞሪንሆ በአሰልጣኝነት ታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ቶተንሀምን ይዘው 10 ጊዜ ሽንፈት አስተናግደዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የትኛውም የፕሪምየር ሊጉ ቡድን በያዝነው የውድድር ዓመት እንደ ቶተንሀም ቀድመው ግብ አግብተው ሽንፈት አላስተናገዱም። ቶተንሃሞች ቀድመው ግብ አስቆጥረው ጀምረው እስካሁን 20 ነጥቦችን ጥለዋል።












