ዩክሬን በሩሲያ የኦንላየን እቃዎች መሸጫ መጋዘን ላይ ከባድ ጥቃት መፈጸሟ ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, social media
የዩክሬን ድሮኖች በሩሲያ ግዙፍ የኦንላየን እቃዎች መሸጫ የሆነውን የዋይልድቤሪስ ሁለት መጋዘኖችን መትተው ስምንት ሰዎች መሞታቸውን እና 62 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሩሲያ ባለሥልጣናት ገለጹ።
ከሞስኮ በስተደቡብ ምሥራቅ በግምት 475 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው የታምቦቭ ከተማ በሚገኝ መጋዘን ውስጥ ሰባት ሰዎች ሲገደሉ 25 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል።
በሞስኮ ክልል በኤሌክትሮስትል በሚገኝ ሌላ የዋይልድቤሪስ መጋዘን ውስጥ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ደግሞ አንድ ሰው ሲገደል 37 ሰዎች ደግሞ ቆስለዋል ተብሏል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ጥቃቶቹ "ማዕቀብ የተጣለባቸውን የድሮን እና ለሃሰሳ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ክፍሎችን ለማቅረብ" ጥቅም ላይ የዋሉ "ዋና ዋና የሎጂስቲክስ ተቋማት" ላይ መፈጸማቸውን ተናግረዋል።
ዩክሬን በአዞቭ ባሕር፣ በጥቁር ባሕር እና በሩሲያ ሥር በምትገኘው ክሪሚያ ውስጥ ዒላማዎችንም መምታቷን አክለዋል።
መጋዘኑ ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ የወጡ ያልተረጋገጡ ምስሎች ከአንድ ሰፊ ሕንፃ የእሳት ነበልባል እና ጥቁር ጭስ ሲወጣ አሳይተዋል።
በርካታ ሰዎችም ወደ መኪና ማቆሚያ ቦታ እየሸሹ ሲሄዱ ታይተዋል።
ዜሌንስኪ እንዳሉት የዩክሬን እርምጃዎች "የሩሲያ ጦር በሲቪል መሠረተ ልማታችን ላይ እንዲሁም በከተሞቻችንና በማኅበረሰባችን ላይ ለሰነዘረው ጥቃት" ምላሽ የሰጡ ናቸው። ረቡዕ ምሽት ላይ በመላው ዩክሬን በተፈጸሙ የሩሲያ ጥቃቶች 14 ሰዎች ተገድለዋል።
ዋይልድቤሪስ እንደ አማዞን ያለ ግዙፍ በኦንላየን እቃዎችን የሚሸጥ የሩሲያ ኩባንያ ነው።
የዋይልድቤሪስ ሥራ አስፈጻሚ ታታይና ኪም ለሩሲያ እና ለኩባንያው “አስቀያሚ ምሽት ነበር” ብለዋል።
የቴምቦቭ ክልል አስተዳዳሪ ኢቪግኒ ፐርቬሾቭ በቴሌግራም ገጻቸው ላይ “በምሽት ፈረቃ እየሰሩ የነበሩ ሰባት ሰዎች እዚያው ተገድለዋል” ሲሉ ጽፈዋል።
አክለውም 25 ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ሰባቱ በከባድ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ብለዋል። አብዛኛው ጉዳት የደረሰው በፍንጥርጣሪዎች መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ይህ በታምቦቭ ክልል ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ ጥቅም ላይ በዋሉት ድሮኖች ብዛት እና በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና የጉዳት መጠን ሲታይ "እጅግ ትልቅ እና ኢ ሰብአዊ" ጥቃት ነበር ብለዋል።




















