አሜሪካ እና ኢራን የአያቶላህ ኻሜኒ የቀብር እስከሚጠናቀቅ ከድርድር እረፍት መውሰዳቸውን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር የምታደርገው ድርድር እየተካሄደ ያልሆነው ሁለቱ አገራት የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሌ ኻሜኒ የቀብር ስነ ስርዓት እስከሚጠናቀቅ በመወሰናቸው መሆኑን ለአክሲዮስ ተናገሩ። ትራምፕ፤ የኻሜኒ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የተወሰኑ ኢራናውያን ሲያለቅሱ በመመልከታቸው እንደተገረሙ ከአሜሪካው የዜና ምንጭ ጋር ባደረጉት የስልክ ቃለ መጠይቅ ገልጸዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. የኢራን ጠቅላይ መሪ ሚስት ቀብር የባለቤታቸው አስከሬን ባልተገኘበት ተፈጸመ

    በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት ከወራት በፊት የተገደሉት የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ባለቤት ዛሃራ ሃዳድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ባላቸው ባልተገኙበት ረቡዕ ዕለት ቴህራን ውስጥ መፈጸሙ ተዘገበ።

    ዛሃራ ሃዳድ አዴል በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት ከተገደሉት የኻሜኒ ቤተሰብ አባላት አንዷ ናቸው። በመጀመሪያው ዕለት የቦምብ ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ እና ሌሎች በርካታ የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት መገደላቸው ይታወሳል።

    በተጨማሪም የአባታቸውን ሥልጣን የተረከቡት የዛሃራ ባለቤት ሞጅታባ ኻሜኒ በጥቃቱ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው በተደጋጋሚ ቢነገርም እስካሁን በተጨባጭ የተረጋገጠ ነገር የለም።

    የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጠቅላይ መሪ ከሆኑ በኋላ የጽሁፍ መልዕክት ከማስተላለፍ ውጪ በይፋ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ በጥቃቱ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

    በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት የተገደሉት የሞጅታባ ሚስት ዛሃራ የሟቹ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አማካሪ እና በእስላማዊው ሪፐብሊክ ውስጥ ተደማጭ የሆኑት ጎላማሊ ሃዳድ አዴል ልጅ ነበሩ።

    ከጥቂት ቀናት በፊት ጎላማሊ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከከፈቱ ወዲህ የሟች ሴት ልጃቸው ባለቤት የሆኑትን ሞጅታባ ኻሜኒን አግኝተዋቸው እንደማያውቁ ተናግረዋል።

  2. “የሆርሙዝ ወሽመጥ የኢራን የማያሻማ ሉዓላዊ ግዛት አካል ነው” - የኢራን ጦር

    ሆርሙዝ ወሽመጥ የማያሻማ የኢራን ሉዓላዊ የውሃ አካል በመሆኑ ለወራሪዎች ቦታ እንደሌለው ኻታም አል-አንቢያ በመባል የሚታወቀው የኢራን ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ማዘዣ ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

    ስለዚህም “ከአሜሪካ በኩል በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የሚደረግ የትኛውም ዓይነት ጠልቃ ገብነት ከኢራን ጦር ኃይሎች ፈጣን እና የማያዳግም ምላሽ ይሰጠዋል” በማለት አስጠንቅቋል።

    ከማዘዣ ማዕከሉ የወጣውን መግለጫ ጠቅሰው የኢራን መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት “ወሳኝ የውሃ ላይ መተላለፊያ የሆነው የሆርሙዝ ወሽመጥ ደኅንነት እና አስተዳደር ጉዳይ የኃያላኑ የእስላማዊት ኢራን ጦር ኃይሎች የማይታለፍ ቀይ መስመር ነው” በማለት አጽንኦት መስጠቱን አመልክተዋል።

    “ሆርሙዝ ወሽመጥ የወራሪዋ አሜሪካ የምትቆጣጠረው መስክ ሳይሆን፣ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የማያሻማ ሉዓላዊ ግዛት ነው” ሲል ኢራን በባሕር መተላለፊያው ላይ ያላትን የበላይነት ገልጿል።

    ሁሉም የንግድ መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ደኅንነታቸው ተጠብቆ በሰላም ለማለፍ በኢራን የተቀመጠውን መስመር ብቻ መከተል እንዳለባቸው እና ካልሆነ ግን የሚገጥማቸውን ቅጣት መቀበል እንደሚገባቸው አስጠንቅቋል።

    ኢራን በአሜሪካ እና በእስራኤል ጦርነት ከተከፈተባት በኋላ በወሳኙ የባሕር መስመር በኩል ላይ በሚያልፉ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር በመጀመሯ ሆርሙዝ ዝግ ሆኖ ቆይቷል።

    ሆርሙዝ ከዓለም ፍጆታ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው ነዳጅ እና ጋዝ ከፋርስ ባሕረ ሰላጤው አገራት በመነሳት የሚተላለፍበት ወሳኝ የባሕር መስመር ነው። በጦርነቱ ወቅት መርከቦች ማለፍ ባለመቻላቸው በዓለም ዙሪያ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ ነበር።

  3. አሜሪካ ጦሯን ከሳዑዲ አረቢያ ለማስወጣት እያሰበች እንደሆነ ተዘገበ

    አሜሪካ በሳዑዲ አረቢያ የሚገኝ ጦሯን ለመቀነስ ወይም የተወሰነውን ወታደራዊ ኃይል ከሳዑዲ አስወጥታ ወደ ሌላ ቦታ ለማዘዋወር እያሰበች እንደሆነ ዋል ስትሪት ጆርናል የተመለከተውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገበ።

    አሜሪካ ይሄንን እርምጃ ለመውሰድ እያሰበች ያለው በዋሽንግተን እና በሪያድ መካከል ያለውን ውጥረት ተከትሎ ነው ተብሏል።

    ሁለቱ አገራት በኢራን ጦርነት እንዲሁም በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ደኅንነት ከማስጠበቅ ጋር በተያያዘ ውጥረታቸው ተባብሷል።

    ዋል ስትሪት ጆርናል የተመለከተው ሪፖርት እንደሚጠቁመው፤ ከ100 በላይ የአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላኖች የሆርሙዝ ወሽመጥ ክፍት ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚገኙ የጦር ሰፈሮች እና ከወታደራዊ መርከቦች በመነሳት በረራ አድርገዋል።

    ይህ ስምሪት ከሳዑዲ አረቢያ ያልተጠበቀ መሰናክል እንደገጠመው ዘገባው ያትታል።

    በሳዑዲ የሚገኙ የጦር ሰፈሮች እና የአገሪቱ የአየር ክልል ለዚህ ስምሪት ከፍተኛ ድርሻ ያለው ቢሆንም ሪያድ ከዋሽንግተን ጋር ለመተባበር አልፈቀደችም።

    ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ የአሜሪካ ባለሥልጣን ለዋል ስትሪት ጆርናል እንደገለጹት፤ የሳዑዲ ተቃውሞ አሜሪካ ‘ኦፕሬሽን ፕሮጀክት ፍሪደም’ የተባለውን ስምሪት እንድታቋርጥ አስገድዷታል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይፋ ያደረጉት ኦፕሬሽን መርከቦች በሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲተላለፉ ለማስቻል ያለመ ነበር።

    አሜሪካ ኦፕሬሽኑን ያቋረጠችው በግማሽ ልብ ሆና ነው ተብሏል።

    አሜሪካ በሳዑዲ ያላትን ጦር ለመቀነስ አልያም የተወሰነ ወታደራዊ ኃይሏን ከሳዑዲ አስወጥታ ወደ እስራኤል ወይም ዮርዳኖች ለማዘዋወቅ ማሰቧን የዋል ስትሪት ዘገባ ይገልጻል።

    በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰም ዘገባው ያትታል።

    አሜሪካ ወታደሮቿን ለማስወጣት ከመወሰኗ በፊት አማራጮችን እንደምትመለከትም ተገልጿል።

    የአሜሪካ ባለሥልጣናት ስለ ጉዳዩ ማረጋገጫም ማስተባበያም አልሰጡም።

  4. ሆርሙዝ በአሜሪካ ሳይሆን በኢራን ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ መታወቅ አለበት - ኢራን

    የሆርሙዝ ወሽመጥ በአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ ዕዝ ሳይሆን በኢራን ቁጥጥር ሥር ነው ሲሉ የአገሪቱ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባባዲ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት ገለጹ።

    የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ማዕከላዊ ዕዝ በኢራን ላይ የሚካሄደውን ወታደራዊ ዘመቻ የሚመራ ሲሆን፣ በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠር እና በኢራን ላይ እስካሁን የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያስተባብር አካል ነው።

    ‘ሴንትኮም’ የተባለው ይህ ወታደራዊ ዕዝ በወሳኙ የባሕር መተላለፊያ ወሽመጥ ላይ ዋነኛ ኃይል ነው። ነገር ግን የኢራን ጦር በአካባቢው ባለው ሉዓላዊነት የተነሳ በቀጣናው መርከቦች እንዳይንቀሳቀሱ ለማገድ ችሎ ቆይቷል።

    በዚህም የተነሳ ኢራን በመተላለፊው ላይ ያላትን ቁጥጥር ለማጥበቅ ሕግ እስከማውጣት ደርሳለች። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ከአሜሪካ ጋር እየተካሄደ ያለው ንግግር ኢራን በሆርሙዝ ላይ ያላትን የበላይነት አሳልፎ የሚሰጥ አለመሆኑን አስረግጠው ገልጸዋል።

    ጋሪባባዲ ጨምረውም "ባህሬን ውስጥ የሚካሄደው ወታደራዊ ውይይት የባሕረ ሰላጤውን ደኅንነት የተመለከተ ሕጋዊ አሠራርን የሚፈጥር አይደለም። ከዚያ ይልቅ የቀጣናው ደኅንነት የሚረጋገጠው የአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ሲያበቃ እና ከአካባቢው ስትወጣ፣ የአገራት ሉዓላዊነት ሲከበር እንዲሁም ከአሜሪካ የበላይነት ውጪ አዲሱን ጂኦፖለቲካዊ እውነታን በመቀበል ነው” ብለዋል።

    ባለፉት ወራት ተዘግቶ ቆይቶ ከሳምንት በፊት የተከፈተው ሆርሙዝ ወሽመጥ አሁንም ደኅንነቱ የተጠበቀ ባለመሆኑ ማኅበራት እና የመርከብ ኩባንያዎች መተላለፊያው “የጦርነት ቀጣና” ሆኖ መታየቱ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል።

    ሆርሙዝ መጀመሪያ ላይ በዚህ ምደባ ውስጥ የተካተተው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ከቀናት በኋላ በመርከቦች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ ነበር። አሁንም በመርከቦች ላይ አልፎ አልፎ ጥቃቶች እየተፈጸሙ በመሆናቸው ነው ስጋቱ የተፈጠረው።

  5. ኢራን እና አሜሪካ ውይይት ለመቀጠል መስማማታቸውን ኳታር ገለጸች

    በኳታር ዶሃ ሲካሄድ የነበረው የኢራን እና የአሜሪካ ልዑካን ቀጥተኛ ያልሆነ ውይይት መጠናቀቁን የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማጂድ አል-ናስሪ ተናግረዋል።

    “ተደራዳሪዎቹ ምክክር እና ውይይት ለመቀጠል ተስማምተዋል። ቀጣዩ ውይይት መቼ እንደሚካሄድ በተቻለ ፍጥነት የሚገለጽ ይሆናል” ብለዋል።

    ውይይቱ “በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ” መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።

    ፕሬዝዳንቱ በፓኪስታን እና በኳታር አሸማጋዮች በኩል የተደረገውን ንግግር “እጅግ ጥሩ ስብሰባ” ሲሉ ገልጸው “ለውጥ እየታየበት ነው” ብለዋል።

    ቴህራን ወደ ውይይት ወይም ድርድር ለመመለስ ዕቅድ እንዳልያዘች ገልጻ የነበረ ቢሆንም፤ ከአሜሪካ ልዑካን ጋር ቀጥተኛ ባልሆነ ውይይት ላይ ልዑካኖቿ መላኳ ተገልጿል።

    የኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካዜም ጋሪባልባዲ በዶሃው ውይይት “የተቆጣጣሪው ቡድን ቀጥተኛ የግንኙነት መስመር ነገ እንዲከፈት” ተስማምተናል ብለዋል።

    “የመግባቢያ ሰነዱ ጥሰት በይፋ ይመዘገባል፣ ውይይት ይደረግበታል፣ ውሳኔም ይሰጥበታል” ሲሉም አክለዋል።

  6. “በዲፕሎማሲው ወይም በጦርነቱ የማታግዙን ከሆነ አታስቸግሩን”- የኢራን ባለሥልጣን

    የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ ከአገራቸው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ከአሜሪካ ጋር ስለሚደረገውን ድርድር ከቴህራን የሚነሱ ውስጣዊ ትችቶችን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “በዲፕሎማሲው ወይም በጦርነቱ የማታግዙን አታስቸግሩን” ብለዋል።

    በቃለ ምልልሱ ላይ ከኢራን የሚነሱ ውስጣዊ ትችቶችን በተመለከተ ጠንካራ ንግግሮችን አድርገዋል።

    ስዊትዘርላንድ በተደረገው ድርድር፤ እገዳ ተጥሎበት የነበረውን የኢራን ሃብት የሚያስመልስ ሰነድ መጠናቀቁን ገልጸዋል። በዚህ ውይይት ላይ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ እንዲሁም የአሜሪካ ግምጃ ቤት ምክትል ጸሐፊ መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።

    ከአሜሪካ ጋር ስለሚደረገው ድርድር እና ስለ ተደራዳሪው ቡድን የሚነሱ የአገር ውስጥ ትችቶችን በተመለከተ ደግሞ “በዲፕሎማሲው ወይም በጦርነቱ የማታግዙን ከሆነ አታስቸግሩን፤ የትራምፕን ንግግር መድገም አቁሙ. . . በጎ አይደለም። ሕዝቡ እንዲረጋጋ እና በኢስላሚክ ሪፐብሊኳ ደስተኛ እንዲሆን ተውት” ብለዋል።

    የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ተወካዮች ወደ ኢራን የመግባታቸውን ጉዳይ በተመለከተ “በምክር ቤት ባስተላለፍነው ውሳኔ እና ጠቅላይ የብሔራዊ ደኅንነት ካውንስሉም ባሳለፈው ውሳኔ መሠረት ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎችን በማንኛውም ሁኔታ መመልከት አይቻለም” ብለዋል።

    በሌላ በኩል አሜሪካ እና ኢራን በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ እያደረጉ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር “በጥሩ ሁኔታ” እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ገልጸዋል።

  7. ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ እና ኢራን ተደራዳሪዎች ንግግር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ተናገሩ

    አሜሪካ እና ኢራን በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ እያደረጉ ያሉት ቀጥተኛ ያልሆነ ንግግር በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።

    ፕሬዝዳንቱ በፓኪስታን እና በኳታር አሸማጋዮች በኩል የሚደረገውን ንግግር “እጅግ ጥሩ ስብሰባ” ሲሉ ገልጸውታል።

    ወደ ሰሜን ዳኮታ ግዛት ከመብረራቸው በፊት ከጋዜጠኞች ጋር የተነጋገሩት ትራምፕ፤ “ኢራንን ከኒውክሌር ነጻ የማድረግ ሂደት በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው” ብለዋል።

    የኒውክሌር ጦር መሣሪያ የመገንባት ዕቅድ አላት የሚል ክስ የሚቀርብባት ኢራን፤ የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ለሰላማዊ ዓላማ ብቻ እንደሚል በተደጋጋሚ ገልጻለች።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ “በጣም ጥሩ ስብሰባዎችን አድርገዋል፤ [የሚሆነውን] እናያለን” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። “እጅግ በኃይለኛው መትተናቸዋል…ሆኖም በጣም በጥሩ ሁኔታ እየተቀራረብን ነው” ሲሉም ተደምጠዋል።

    ኳታር ውስጥ እየተደረገ ባለው ቴክኒካዊ ንግግር ላይ የአሜሪካ እና ኢራን ባለሥልጣናት ፊት ለፊት ለድርድር አልተቀመጡም።

    የአሜሪካ ዋነኛ ተደራዳሪ የሆኑት የፕሬዝዳንቱ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የ ትራምፕ አማች ጃሬድ ኩሽነር ወደ ዶሃ ተጉዘዋል።

    የሁለቱ አገራት ተደራዳሪዎች ንግግር ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን ተኩስ ልውውጥ ተከትሎ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ የሚያስችሉ ነጥቦችን በአሸማጋዮች አማካኝነት አንዳቸው ለሌላቸው ያቀርባሉ።

  8. የሜክሲኮ ብሔራዊ ቡድን በማሸነፉ አደባባይ ከወጡ ደጋፊዎች ሦስቱ ሕይወታቸው አለፈ

    በዓለም ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ኢኳዶርን የገጠመችው ሜክሲኮ በአሸናፊነት ወደ ቀጣዩ ዙር በማለፏ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡ የአገሪቱ ዜጎች መካከል የሦስቱ ሕይወት አለፈ።

    ደጋፊዎቹ ሕይወታቸው ያለፈው፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ በወጡባት ዋና ከተማዋ ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ በተፈጠረው መገፋፋት ነው። ሕይወታቸው ያለፈው የ19 እና የ48 ዓመት ሴቶች እና የ44 ዓመት ወንድ ናቸው።

    የከተማዋ የጤና ባለሥልጣናት እንዳሉት የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያዎች ራሳቸውን ስተው የነበሩትን ሦስቱን ሰዎች ለመርዳት ሙከራ ከተደረገ በኋላ ለተጨማሪ ሕክምና ወደ ሆስፒታል ተልከው ሕይወታቸው እዚያ አልፏል።

    ከአሜሪካ፣ ከካናዳ ጋር በጋራ የዓለም ዋንጫን እያስተናገደች ያለችው ሜክሲኮ ኢኳዶርን ሁለት ለዜሮ በሆነ ውጤት ካሸነፈች በኋላ የአገሪቱ ዜጎች በደስታ ሰክረው ወደ አደባባይ ወጥተዋል።

    በሜክሲኳዊያን ዘንድ ይህ ከፍተኛ ደስታ የተፈጠረው አገራቸው ከአውሮፓውያን 1986 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥሎ ማለፍ በመድረሷ ነው።

    ሦስት ሰዎች የሞቱበት ሁኔታ ከተከሰተ በኋላ የሜክሲኮ ሲቲ ከንቲባ ክላራ ብሩጋዳ ሕይወታቸው ላለፈ ሰዎች ቤተሰቦች ሐዘናቸውን ገልጸው፣ የአገሪቱ ዜጎች ደስታቸውን ሲገልጹ “በኃላፊነት እና በጥንቃቄ” እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

    ሜክሲኮ 32 ቡድኖች ከሚገኙበት ጥሎ ማለፍ በመሻገር ወደ 16ቱ ምድብ ተቀላቅላለች። በቀጣይ ደግሞ ዛሬ ረቡዕ ምሽት እንግሊዝ እና ዲሞክራቲክ ኮንጎ በሚያደርጉት ጨዋታ ከሚያሸንፈው ቡድን ጋር ትጋጠማለች።

  9. በቬንዙዌላ መሬት መንቀጥቀጥ ለስድስት ቀናት ተቀብሮ የነበረ የሦስት ዓመት ልጅ በሕይወት ተገኘ

    በቬንዙዌላ ባጋጠመው የመሬት መንቀጥቀጥ ለስድስት ቀናት ፍርስራሽ ውስጥ ተቀብሮ የቆየ የሦስት ዓመት ልጅ በሕይወት መገኘቱን በስፍራው እየተንቀሳቀሰ ያለ የነፍስ አድን ቡድን አስታወቀ።

    ክሊበር ሞራን የተባለ ህጻን ላ ጉዋይራ ግዛት ውስጥ ከፍርስራሽ ስር መውጣቱን የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ ተናግረዋል። ጊዜያዊ ፕሬዝዳንቷ የህጻኑን በሕይወት መገኘት "የሕዝባችን የጥንካሬ እና የተስፋ ምንጭ" ሲሉ ገልጸውታል።

    ባለፈው ሳምንት የተከሰቱት በሬክተር ስኬል 7.2 እና 7.5 ሆነው የተለኩ ሁለት የመሬት መንቀጥቀጦች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ወደ 1,943 አድጓል። ከ10,000 በላይ ሰዎች የተጎዱ ሲሆን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ያሉበት አልታወቀም።

    ከአሜሪካው የጠፈር ምርምር ተቋም የናሳ የተገኘ የሳተላይት መረጃ ላይ የተደረገ የመጀመሪያ ደረጃ ምርመራ እንደሚያሳየው፤ በመሬት መንቀጥቀጡ 58,870 ገደማ ሕንጻዎች እንደተጎዱ ወይም ሙሉ በሙሉ እንደፈረሱ ተገምቷል።

    የሦስት ዓመቱን ልጅ ያገኘው የዮርዳኖስ ሲቪል መከላከያ ቡድን እንዳስታወቀው፤ ሕጻኑ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና ተደርጎለት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል። የልብ ምት እና ስትንፋስን ጨምሮ መሰል መሠረታዊ የጤና ሁኔታው ጥሩ ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል።

    በመሬት መንቀጥቀጥ የተቀበሩ ሰዎች ከፍተኛ የሆነ በሕይወት የመገኘት ዕድል ያላቸው በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ውስጥ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገናራሉ። ሕጻኑ በሕይወት ከፍርስራሽ ስር የወጣው ከዚህ ጊዜ ከተጨማሪ ሦስት ቀናት በኋላ ነው።

    በመሬት መንቀጥቀጥ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ስፍራዎች አንዱ ላ ጉዋይራ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን ሰዎችን የማዳን ስራ ላይ ተሰማርተዋል።

    የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ ላ ጉዋይራ ውስጥ መጠነ ሠፊ የምግብ እጥረት እንደተከሰተ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች እንደሌሉ እንዲሁም የኮሚዩኒኬሽን መስመሮች በከፍተኛ ደረጃ መቋረጣቸውን አስታውቋል።

  10. በፓኪስታን የሕጻናት ማሠልጠኛ ጣሪያ ተደርምሶ 14 ልጆች ሞቱ

    በፓኪስታን በሚገኝ የግል የሕጻናት ማሠልጠኛ ተቋም ጣሪያ ተደርምሶ 14 ልጆች መሞታቸው ተገለጸ።

    ጣሪያው ለምን እንደተደረመሰ ምርመራ የተከፈተ ሲሆን፤ በተቋሙ ውስጥ የነበሩት ሕጻናት ከ10 ዓመት በታች መሆናቸው ተገልጿል።

    ከክስተቱ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

    የድንገተኛ ጊዜ አገልግሎት የሚሰጠው ሬስኪው 1122 ቃል አቀባይ ፋሩቅ አሕመድ ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ሕጻናቱን ከሕንጻው ለማውጣት አንድ ሰዓት ወስዷል።

    ተጨማሪ አምስት ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸውም ይገመታል።

    ከተጎጂዎቹ አንዷ የእህቱ ልጅ እንደሆነች የገለጸ ግለሰብ ሕንጻው “ተዳክሞ” እንደነበር ተናግሯል።

    ልጆቹ እየተማሩ ሳለ ለሕንጻው ጥገና እየተደረገ እንደነበረም ገልጿል።

    “ድንገት ሕንጻው ተደረመሰ። የተወሰኑ ልጆች አናት ላይ ነው የወደቀው። ጣሪያውን ስለተጫኑት ተደርምሷል” ሲልም ክስተቱን ገልጿል።

    የፓኪስታን ጠቅላይ ሚኒስትር በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

  11. "ድርድሮች ስኬታማ ከሆኑ በዘላቂነት የተለወጠች ኢራንን ታያላችሁ"- ጄዲ ቫንስ

    የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃል ምልልስ “አሜሪካ ከኢራን ጋር በጣም ጥሩ ነጥብ ላይ እንደምትገኝ” ተናገሩ።

    ከኢራን ጋር የሚደረጉ ድርድሮች ስኬታማ ከሆኑ "የተለወጠች ኢራንን ትመለከታላችሁ" ብለዋል።

    “በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ኢራናውያን መርከብ ላይ ጥቃት አላደረሱም። በሆርሙዝ ወሽመጥ በኩል ነዳጅ እያለፈ ነው። ምክንያቱም ኢራናውያን መርከብ ላይ ጥቃት ቢፈጽሙ የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጡ ፕሬዝዳንቱ በግልጽ ተናግረዋል” ሲሉም ገልጸዋል።

    ቫንስ በቃለ ምልልሳቸው “ከኢራን ጋር የሚደረጉ ድርድሮች ስኬታማ ከሆኑ፣ ስኬታማ እንዲሆኑም እንፈልጋለን፣ በዘላቂነት የተለወጠች ኢራንን የምትመለከቱ ይሆናል” ብለዋል።

    “የተለወጠች” ብለው የገለጿት ኢራን ቀጣናዊ ሽብር እና አለመረጋጋት እንደማትደግፍ እንዲሁም በዘላቂነት የኒውክሌር ፍላጎቷን እንደምትሰርዝ ገልጸዋል።

    “በዚህም ምክንያት የዓለም ምጣኔ ሃብት ዳግመኛ ይቀበላታል። ይህም ለአሜሪካውያን እና መላው ቀጣና ጥሩ ውጤት ነው” ብለዋል።

    ጄዲ ቫንስ አክለውም “የተገባ ባህሪ ካላሳዩ እና ማየት የምንፈልገውን ለውጥ ካላመጡ የኒውክሌር መርሃ ግብራቸው ይወድማል፤ ወታደራዊ አቅማቸው ይንኮታኮታል። አሜሪካ ከእነሱ አንጻር ጠንካራ ናት” ብለው ተናግረዋል።

  12. የአሜሪካ ልዑካን በዶሃ የኢራንን ባለሥልጣናት ባያገኙም ከአደራዳሪዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ተገለጸ

    የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እና የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የልጃቸው ባለቤት ጃሬድ ኩሽነር በዶሃ ከአደራዳሪዎች ጋር እንደሚገናኙ የኳታር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ተናገሩ።

    የአሜሪካ ልዑካን ከአሸማጋዮች ጋር ቢወያዩም ከኢራን ባለሥልጣናት ጋር እንደማይገናኙ ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

    ቃል አቀባዩ ማጅድ አል-አንሳሪ እንደተናገሩት በቀጣይ ቀናት በአሜሪካ እና በኢራን መካከል በከፍተኛ ባለሥልጣናት ደረጃ ቀጥተኛ ውይይት ወይም ንግግር አይኖርም።

    ሁለቱ አገራት ለአራት ቀናት አንዳቸው በሌላቸው ላይ ሲሰነዝሩ የነበረውን ጥቃት አቁመው ልዑካንን ወደ ዶሃ ለመላክ ተስማምተዋል።

    ጥቃት መሰናዘር መጀመራቸው የመግባቢያ ሰነዱን አደጋ ውስጥ ይጥላል በሚል ተሰግቷል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት አራት ወራት የዘለቀ ጦርነት በመግባቢያ ሰነዱ አማካኝነት መገታት ችሏል።

    ኢራን እና አሜሪካ ከሁለት ሳምንት በፊት ስምምነቱን የፈረሙት በፓኪስታን እና ኳታር አሸማጋይነት ነበር።

    ቢያንስ በ60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ በዘላቂነት ግጭት ለማቆም እና ለኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እልባት ለመስጠት ተስማምተዋል።

    በስዊትዘርላንድ በተካሄደው የመጀመሪያ ሳምንት ድርድር አበረታች ውጤት እንደታየ ፓኪስታን እና ኳታር ገልጸዋል።

  13. በጋና በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ቢያንስ 13 ሰዎች ሞቱ

    በጋና መዲና አክራ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ቢያንስ 13 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ የእሳት አደጋ መከላከያ መሥሪያ ቤት አስታወቀ።

    በቀጣይም ከአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል መነሻውን ያደረገ አውሎ ንፋስ እና ዝናብ ሊኖር ስለሚችል ዜጎች ከቤት እንዳይወጡ ወይም ከፍ ያለ ሥፍራ ላይ እንዲሆኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

    ካለፈው እሑድ ዝናብ የተከማቸ ውሃ መጠኑ እየቀነሰ ቢመጣም የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ተገልጿል።

    በተለይም ዝቅተኛ አካባቢዎች ለአደጋ ተጋላጭ ሆነዋል።

    በማኅበራዊ ሚዲያ የታዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ቤቶች እና ተሽከርካሪዎች በጎርፍ ተውጠው ያሳያሉ፤ ሕንጻዎች ላይም ጉዳት ደርሷል።

    በጎርፍ ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ፖሊስ እና የእሳት አደጋ ተከላካዮችን ጨምሮ የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ተሰማርተዋል።

    የጋና የአገር ውስጥ ሚኒስቴር እንዳለው ያለውን ሁኔታ እንዲከታተሉ እና የሰዎችን ሕይወት እንዲሁም ንብረት እንዲያድኑ ሠራተኞቹ ተሰማርተዋል።

    እስካሁን 470 ሰዎችን ማትረፍ እንተቻለ ተገልጿል።

    በጎርፉ ምክንያት በአክራ የሚገኝ የፕላስቲክ ፋብሪካ ውስጥ እሳት ተነስቷል።

  14. ዋትስአፕ ስልክ ቁጥር ሳይታይ በ‘ዩዘርኔም’ ብቻ መነጋገርን ሊፈቅድ ነው

    የመልክዕክት መለዋወጫ መተግበሪያ የሆነው ዋትስአፕ፤ ተጠቃሚዎች ‘ዩዘርኔም’ ብቻ በመለዋወጥ ቁጥራቸውን ሳይታወቅ ከሰዎች ጋር እንዲነጋገሩ ሊፈቅድ ነው።

    በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስት ቢሊዮን ተጠቃሚዎች ያሉት ዋትስአፕ፤ ይህ አሠራር በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን ገልጿል።

    ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ግን ተጠቃሚዎች መለያ የሚሆናቸውን ‘ዩዘርኔም’ እንዲመርጡ ፈቅዷል። ይህንን መለያ ማስቀመጥ ግዴታ እንዳይሆን ተነግሯል።

    ተቋሙ እንደገለጸው፤ ተጠቃሚዎች ባሻቸው ጊዜ ‘ዩዘርኔሙን’ ማጥፋት ወይም መቀየር ይችለሉ።

    አሠራሩ ተግባራዊ መሆን ሲጀምር የዋትስአፕ ተጠቃሚዎች ‘ዩዘርኔም’ ብቻ በመለዋወጥ ከሰዎች ጋር መነጋገር ይችላሉ። የማይፈለጉ መልዕክቶችን ‘ብሎክ’ የማድረጊያ አማራጭ አሁንም ቢሆን ይቀጥላል።

    ተጠቃሚዎች የሚመርጡት ስም ከ35 ፊደላት ያነሰ መሆን አለበት። እጅግ ታዋቂ የሆኑ ሰዎችን ስም ግን ሌሎች ተጠቃሚዎች እንዲጠቀሙበት አይፈቀድም።

  15. በደቡብ አፍሪካ ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ምክንያት የፀጥታ ኃይሎች ከፍተኛ መጠን ተሰማሩ

    ዛሬ ማክሰኞ በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ከተሞች የሚደረገው ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ ወደ አመጽ ሊያመራ ይችላል በሚል ስጋት በመላ አገሪቱ በርካታ የፖሊስ አባላት ተሰማርተዋል።

    የተቃውሞ ሰልፉ የሚካሄደው፤ ፀረ ስደተኛ የሆኑ ቡድኖች ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸው የውጭ አገር ዜጎች አገሪቱን ለቅቀው እንዲወጡ ያስቀመጡት ይፋዊ ያልሆነ ቀነ ገደብ ዛሬ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው።

    ተቃውሞ ሊካሄድ ከታቀደባቸው ከተሞች አንዷ የሆነችው ጆሃንስበርግ ባልተለመደ ሁኔታ ፀጥታ ነግሶባታል።

    ሰልፍ በሚካሄድባቸው ጎዳናዎች የሚገኙ መደብሮች ተዘግተዋል። የፖሊስ አባላት በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ይታያሉ።

    ጆሃንስበርግ ውስጥ ከሚገኙ ትልቅ ስፍራዎች አንዱ በሆነው ሶዌቶ ውስጥ የውጭ አገር ዜጋን መደብር ዘርፈዋል የተባሉ አምስ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ፖሊስ አስታውቋል።

    ኩዋዙሉ ናታል ግዛት ውስጥ ደግሞ ሱቅ ሰብረው በመግባት የተወነጀሉ አምስት ሰዎች ታስረዋል። የግዛቱ ዋና ከተማ በሆነችው ደርባን ውስጥ በርካታ የንግድ ማዕከላት ተዘግተዋል።

    የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ ሰልፈኞች በሰላማዊ እና ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ እንዲንቀሳቀሱ በተደጋጋሚ አስጠንቅቀዋል።

  16. የኢራኑ ጠቅላይ መሪ በድርድሮች ውስጥ ያልተቋረጠ ተሳትፎ እንደነበራቸው ተነገረ

    ኢራን ከአሜሪካ ጋር እየተደረጉ ያሉ ድርድሮች በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ተመሥርተው በጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ ሙሉ ተሳትፎ እየተካሄደ መሆኑን ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን ተገናሩ።

    ፕሬዝዳንቱ ቆም በተባለችው ከተማ ውስጥ ከሃይማኖት መምህራን ጋር ባደረጉት ስብሰባ፤ ከአሜሪካ ጋር የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም የተደረሰው ስምምነት ለኢራን “ዲፕሎማሲያዊ ድል” ነው ብለዋል።

    ጨምረውም አንዳንድ ዘገባዎች በኢራን መሪዎች መካከል ልዩነት እንዳለ አስመስለው ማቅረባቸውን ተችተው “የአገሪቱን የአቋም አንድነት” ለማስጠበቅ ሲባል ምላሽ ከመስጠት መቆጠባቸውን አመልክተዋል።

    ኢራን እና አሜሪካ የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላ በኢራን መንግሥት ውስጥ ያሉ አንጃዎች እና ታዋቂ ሰዎች ስምምነቱን አጥብቀው ሲተቹ ነበረ።

    ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ ስምምነቱን በተመለከተ መልዕክታቸውን ካስተለላፉ በኋላ የሚሰነዘረው ትችት በእጅጉ ጠንክሮ ተሰምቷል።

    በተለይ ደግሞ ከስምምነቱ በኋላ ከተቃዋሚዎች መካከል አንዱ በድርድሩ እና በአመራር ኃላፊነት ላይ ተገቢውን ሚና አልተጫወቱም ያሏቸውን መሪዎች ለመግደል ከዛቱ በኋላ ጉዳዩ በእጅጉ ተካርሮ ነበር።

  17. ስምምነቱ ከተጣሰ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን - ኢራን

    ከአሜሪካ በተደረሰው ስምምነት ላይ የትኛውንም ዓይነት ጥሰት በሚፈጸምበት ጊዜ ኢራን “ያለምንም ጥርጥር ተገቢ እና አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ምላሽ ትሰጣለች” ሲሉ የአገሪቱ ተጠባባቂ የመከላከያ ሚኒስትር ተናገሩ።

    የኢራን መንግሥት ይፋዊ የዜና ወኪል ኢርና እንደዘገበው ሚኒስትሩ ማጂድ ሬዛ ይህንን የተናገሩት ከኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከያ ሚኒስትር ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት ላይ ነው።

    የኢራን ተጠባባቂ ሚኒስትር የባሕረ ሰላጤው አገር ከሆነችው ኳታር ጋር አገራቸው የመከላከያ ትብብር ለማስፋት ያላትን ዝግጁነትም ገልጸዋል።

    ነገር ግን የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሟትን አሜሪካንን በጥርጣሬ እንደሚመለከቱ “ጠላታችንን አናምንም ጣቶቻችን ከመሳሪያችን ቃታ ላይ አይነሱም” ሲሉ ተናግረዋል።

    በየካቲት ወር መጨረሻ ገደማ አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ኢራን ኳታር ውስጥ ያሉትን ጨምሮ ሌሎች ዒላማዎችን በአጸፋ ጥቃት መትታለች።

    የኢራኑ ባለሥልጣን “ቀጣናው የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ መሆን የለበትም፣ የውጭ ኃይሎች በአካባቢው መኖራቸው ደኅንነትን የሚፈጥር ሳይሆን፤ አለመግባባትን፣ አለመተማመንን እና የደኅነንት ስጋትን ያስከትላል” ሲሉ በአካባቢው ያሉትን የአሜሪካ ኃይሎችን ከስሰዋል።

    አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በተለይም በኳታር፣ በኩዌት እና በባህሬን ውስጥ የባሕር እና አየር ኃይል ጦር ሰፈሮች ያሏት ሲሆን፣ በጦነርቱ ወቅትም የኢራን ጥቃት ዒላማዎች ሆነው ቆይተዋል።

    ኳታር በአሁኑ ጊዜ ከፓኪስታን ጋር በመሆን ኢራን እና አሜሪካ ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥረት እያደረገች ነው።

  18. ኢራን ከታገደባት ሀብት ውስጥ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ሊለቀቅላት እንደሆነ ገለጸች

    ኢራን እንዳይንቀሳቀስ ከታገደባት 12 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ግማሹ ሊለቀቅ መሆኑን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዜሽኪያን ተናገሩ።

    አሜሪካ እና ኢራን አራት ወራት ያለፈውን ጦርነት ለመቋጨት በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ከሰፈሩ ጉዳዮች መከካል የኢራን የታገደ ሀብት መለቀቅ አንዱ ነው።

    እስካሁን ሲደረጉ በነበሩ ንግግሮች ላይ ኢራን ጫና ውስጥ ላለውን ኢኮኖሚዋ እረፍት የሚያስገኘው ይህ ሀብት እንዲለቀቅ አጥብቃ ስትጠይቅ ቆይታለች።

    ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት የተፈረመው ሰነድ እንደሚገልጸው አሜሪካ “የታገዱ የኢራን ገንዘብ በሙሉ የማስለቀቅ” ኃላፊነትን ተቀብላለች።

    ትናንቱ ሰኞ ከአገሪቱ ታዋቂ የሃይማኖት አባቶች እና የእስልምና ሕግ ሊቃውንት ጋር ለመገናኘት ወደ ቆም ከተማ ያመሩት የኢራን ፕሬዝዳንት ፔዜሽኪያን፤ ከሀብቱ ውስጥ ግማሽ ያህሉ ሊለቀቅ እንደሆነ አመልክተዋል።

    ፕሬዝዳንቱ፤ “ኳታር ውስጥ ከሚገኘው አጠቃላይ 12 ቢሊዮን ዶላር የኢራን ሀብት ውስጥ ስድስት ቢሊዮን ዶላሩ ተለቅቆ ወደ አገር እንደሚመለስ” መናገራቸውን ኢርና የዜና ወኪል ዘግቧል። ቀሪውን ሀብት ለማስለቀቅ የሚደረገው ጥረት አሁንም እንደቀጠለ ገልጸዋል።

    በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ፤ አሜሪካ ለተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት “ታማኝ ሆና የምትቀጥል ከሆነ” ኢራንም “ግዴታዎቿን እንደምትወጣ” ገልጸዋል።

    ኢራን ሀብቱ ሊለቀቅላት እንደሆነ ብትናገርም እስካሁን ድረስ ስለ ጉዳዩ ከአሜሪካ በኩል ማረጋገጫ አልተሰጠም።

    ይሁን እንጂ ሁለቱ አገራት በተፈራረሙበት ወቅት ማብራሪያ የሰጡ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን፤ ቀጣይ ድርድር በሂደት ላይ እያለ ከኢራን ሀብት ውስጥ የተወሰነው ሊለቀቅ እንደሚችል አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናግረው ነበር።

    ኢራን የመግባቢያ ስምምነቱ እንደተፈረመ ውዲያውኑ ሀብቱ እንዲለቀቅላት ፈልጋ የነበረ ቢሆንም ኋላ ላይ ግን “ግዴታዎቿን ከተወጣች ብቻ ከሀብቷ ከፊሉን ማግኘት እንደምትችል” መቀበሏን ገልጸዋል።

  19. ዴሞክራቲክ ኮንጎ የኢቦላ ሥርጭትን ለመግታት በዋና ከተማዋ የሚደረጉ የሕዝብ ኹነቶችን አገደች

    የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የአገር ውስጥ ሚኒስቴር፤ የኢቦላ ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት ሲባል ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ እና በሌሎች ሦስት ከተሞች ውስጥ ሰዎች የሚሰበሰቡባቸው ኹነቶች እንዳይካሄዱ ክልከላ መጣሉን አስታወቀ።

    በአገሪቱ የተከሰተው የገዳዩ በሽታ ወረርሽኝ እስካሁን ድረስ ከዋና ከተማዋ 1,800 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በሚገኙት በሦስት ምሥራቃዊ ግዛቶች ውስጥ መሠራጨቱ ተረጋግጧል። ባለሥልጣናቱ በሽታው 18 ሚሊዮን ነዋሪዎች ባሏት ኪንሻሳ ውስጥም ሊሠራጭ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።

    ተመሳሳይ ዕገዳ ተጣለባቸው ሌሎቹ ሦስት ከተሞች ኢቦላ መገኘቱ ከተረጋገጠባቸው አካባቢዎች ጋር ይጎራበታሉ።

    የዴሞክራቲክ ኮንጎ ታዋቂ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች እርምጃው በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ሊካሄድ የታቀደውን የተቃውሞ ሰልፍ ለማደናቀፍ ያቀደ ነው በሚል ተቃውመውታል።

    ‘ላሙካ’ የተሰኘው የተቃዋሚ ጥምረት ቃል አቀባይ ፕሪንስ ኢፔንጌ፤ በበሽታው ኪንሻሳ ውስጥ መከሰቱ ባለመረጋገጡ የመንግሥት ውሳኔ “ፖለቲካዊ” ነው ሲሉ ተችተዋል። “ሕጋዊ አይደለም። ይህንን ውሳኔ ልንቀበል አንችልም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

    ‘ኤንቮል’ የተሰኘው ሌላ የተቃዋሚ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ደግሞ፤ ተቃዋሚዎች እገዳውን ችላ በማለት ሰልፉ ላይ እንዲገኙ አሳስበዋል። የተላለፈው ትዕዛዝ “ከሕብረተሰብ ጤና ውሳኔነት ይልቅ ፖለቲካዊ እርምጃ ነው” ብለዋል።

    የዴሞክራቲክ ኮንጎ መንግሥት ስለቀረበው ትችት እስካሁን ምላሽ አልሰጠም።

    በሚቀጥለው ሳምንት እንዲካሄድ የታቀደው ሰልፍ የተዘጋጀው ‘ሲ64’ በተባለው እና በቅርቡ የወጣ ሕግን ለመቃወም በተቋቋመው ጥምረት የተዘጋጀ ነው። ተቃዋሚዎች፤ ሕጉ ፕሬዝዳንቱ ፌሊክ ቲሼኬዲ ከሁለት የሥልጣን ዘመን በላይ በመሪነት እንዲቆዩ እንደሚያስችላቸው ይገልጻሉ።

  20. የቀድሞው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ባይደን፣ ትራምፕን “ከንቱ” ሲሉ ዘለፉ

    በሳምንቱ መጨረሻ በተካሄደ የገቢ ማሰባሰቢያ ላይ ንገግር ያደረጉት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተተኪያቸው ዶናልድ ትራምፕ የሚያስገነቧቸውን “የታይታ ፕሮጀክቶች” በማንሳት “ከንቱ” ሲሉ ዘለፉ።

    ባይደን በቅዳሜ ዕለቱ የዴሞክራቲክ ፓርቲ ዝግጅት ንግግራቸው ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዋይት ሐውስ የግብር አዳራሽ ለመገንባት እንዲሁም የዋሽንግተንን አንጸባራዊ የውሃ ገንዳ ለማደስ የያዙትን ዕቅድ አጣጥለዋል።

    ቢቢሲ የባይደንን ንግግር በተመለከተ ከዋይት ሐውስ አስተያየት ለማግኘት ጥያቄ አቅርቧል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ የቀድሞው መሪ በሥልጣን ላይ ሳሉ የፈጸሟቸውን ተግባራት በተደጋጋሚ ተችተዋል፤ ባይደንም ተመሳሳይ ምላሽ ሰጥተዋል።

    ይሁን እንጂ ባይደን 10 ደቂቃ በቆየው የቅዳሜ ዕለቱ ንግግራቸው ያሰሙት ትችት ከምንጊዜውም የበለጠ ጠንካራ ነበር።

    “የታይታ ፕሮጀክቶቹ ብቻ አይደሉም፤ የግብር አዳራሽ ለመሥራት የዋይት ሐውስ የቀኝ ክንፍን ማፍረሱ፣ በኬኔዲ ሴንተር ሕንጻ ላይ የገዛ ራሱን ለማክበር ስሙን ማስቀመጡ፣ አንጸባራቂውን የውሃ ገንዳ ለመጠገን የራሱን የውሃ ገንዳ ሰው መቅጠሩ ጭምር ነው” ብለዋል።

    “ውይ! እንዴት ያለው ከንቱ [ሰው] ነው” ሲሉም አክለዋል።

    ባይደን በንግግራቸው የጠቀሱት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በ‘ጆን ኤፍ ኬኔዲ ሴንተር ፎር ፐርፎርሚንግ አርትስ’ ሕንጻ የፊት ገጽ ላይ ስማቸውን ለማስፈር ያደረጉትን ሙከራ ነው።

    ፕሬዝዳንቱ ስማቸውን አጽፈው የነበረ ቢሆንም ፍርድ ቤት እንዲወርድ ትዕዛዝ አስተላልፏል።

    ፕሬዝዳንቱ 400 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የግብር አዳራሽ ለመገንባት ሲሉ የቤተ መንግሥቱ የቀኝ ክንፍ እንዲፈርስ በማድረጋቸው የሚቀርብባቸውን ወቀሳ ሲከላከሉ ቆይተዋል።

    ግንባታው የአገር ደኅንነት እና የመንግሥት እንግዳዎችን ለማስተናገድ አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።