ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን ወታደሮች በግዳጅ ለመመልመል የሚደረግ ጥረት ወደ ግጭት እያመራ መሆኑ ተገለፀ
ዩክሬን አምስተኛ ዓመቱን የያዘውን የሩሲያን መጠነ ሰፊ ወረራ እንዲዋጉ ወታደሮችን ለመመልመል ፈተና እንደገጠማት ተገለፀ።
የዩክሬን ጦር በመልማይ ወታደሮች ላይ የሚፈፀም ጥቃት አሁን ላይ መደበኛ እና ትልቅ ችግር መሆኑን ገልጿል።
የቅርብ ጊዜው የብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት ሪፖርት እስካሁን ድረስ በመልማይ መኮንኖች ላይ የደረሱ ከ600 በላይ ጥቃቶችን መዝግቧል። ጥቃቱ "አስጊነቱ እየጨመረ መምጣቱንም" አስጠንቅቋል።
የመጀመሪያው ትልቅ ክስተት ያጋጠመው ሚያዝያ ወር ላይ ሲሆን፣ በርካታ መልማዮች በስለት ጥቃት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ መካከል የአንዱ ሕይወት አልፏል።
በዚህ ወርም በሊቪቭ በቁጥር 200 የሚደርሱ ተቃዋሚዎች የፖሊስ መኮንኖችን በመክበብ ለመያዝ የሞከሩ ሲሆን መኪናቸውን ገልብጠው አውድመዋል።
ይህ አመጽ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ፣ ብሔራዊ አገልግሎት እየሰጡ ባሉ ወታደሮች ላይ የሚፈፀመውን ጥቃት አውግዘዋል።
ዜሌንስኪ "ከዩክሬን የጦር አዛዥ ጋር ባጋጠመው የባህሪ እና የራዕይ ግጭት" ምክንያት ወጣቱን የመከላከያ ሚኒስትር ሚካኼሎ ፌዶሮቭን ከኃላፊነታቸው ካባረሩ በኋላ በአገሪቱ ውዝግብ ተነስቷል።
የመከላከያ ሚኒስትሩን መነሳት ተከትሎም በጦሩ ውስጥ ቁጣ ተፈጥሯል። በመዲናዋ ኪየቭም የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በሊቪቭ የገነፈለው ቁጣም ይህንኑ ተከትሎ የመጣ ነው። በርካቶችም በጦርነቱ ላለመሳተፍ እያፈገፈጉ ነው።
ቫሲል ክሩፒች በምሥራቅ ዶንባስ ክልል በተደረጉ ጦርነቶች የተከሰቱ አስፈሪ ትዕይንቶችን ያስታውሳል። አንዳንድ ጊዜ ሲጸልይ፣ አንዳንድ ጊዜ ሲያለቅስ አሳልፏል። በሩሲያ ወታደሮች ከተሰነዘረው ጥቃትም በተአምር ተርፏል።
ነገር ግን ባለፈው ታኅሣሥ ከጦር ግንባር ጀርባ ሆኖ እያገለገለ ሳለ በገዛ አገሩ ሰዎች ጥቃት ደርሶበታል።
እርሱ እንደሚለው ጥቃት ያደረሱበትን ሁለቱን ግለሰቦች ሰነዶቻቸውን እንዲያሳዩ ቢጠይቃቸውም የሸሹ ሲሆን፣ ሲከታተላቸው ክፉኛ ተደብድቧል።
በዚህም ምክንያት ስድስት ሳምንታትን በሆስፒታል ውስጥ አሳልፏል።
ወታደሮች የሚደበደቡ ከሆነ ለምንድን ነው የታገልነው ሲልም ጠይቋል።
ትልቅ መነቃቃት ታይቶ የነበረው ከሦስት ዓመት በፊት ዩክሬን በደቡብ ምሥራቅ የሚገኘውን ግዛቷን ለመቆጣጠር የአፀፋ ጥቃት በፈፀመችበት ወቅት ነበር።
ሆኖም አልዘለቀም። ያ ጊዜ ጭካኔ የተሞላበት ንቅናቄ የተጀመረበት ወቅት ነበር።
ይህም ቁጣ አስከትሎ ነበር ይላሉ ተቃዋሚው የፓርላማ አባል ኦሌክሳንደር ሆንቻሬኮ።
"አሁንም እነዚህ ሰዎች በጎዳናዎች ላይ ሰዎችን እያደኑ ነው፤ አንዳንዴ አስገዳጅ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ" ብለዋል።
"ግጭት ወደ ግጭት ነው የሚመራው፤ በጣም ትልቅ ችግር ነው፤ እየባሰም ይሄዳል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።
የጦር ተንታኙ ኢቫን ስቱፓክም በዚህ ይስማማሉ።
"በጦር ግንባር የሰው ኃይል በማጣት ዩክሬን መፈተን ጀምራለች፤ የማያቋርጥ ኪሳራ ነው። የዩክሬን ከፍተኛ እዝ እነዚህን ጎዶሎዎች እንደገና መሙላት ስለነበረበት ንቅናቄ ጀምሯል" ብለዋል።
"ተጨማሪ 500 ተዋጊዎችን ሲፈልጉ ማደን ጀመሩ፣ አንፈልግም ያሉትም በጎዳናዎች ላይ ግጭት ውስጥ ገብተዋል" ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሚካኼሎ ፌዶሮቭ በስድስት ወር የሥራ ዘመናቸው እየጨመረ የመጣውን ይህንን ቀውስ ለማስወገድ ማሻሻያዎችን ማድረግ ጀምረው ነበር።
የጦር አገልግሎት በጣም ተወዳጅ እንዲሆንም አድርገው ነበር።
ፌዶሮቭ አዲስ ተመልማዮች መሳተፍ በሚፈልጉበት እንዲሳተፉ አማራጭ በመስጠት እና ለውስን ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ እንዲሁም በተለይ አደጋ ባላቸው ኃላፊነት ላይ ለሚሰማሩ የተሻለ ደመወዝ ለመስጠት አቅደው ነበር።
አስገዳጅ ምልመላን ማስቀረትም ማድረግ ከሚፈልጓቸው ተግባራት አንዱ የነበረ ሲሆን ገና ጅምር ላይ ሳሉ ከሥልጣናቸው ተባርረዋል።
ዩክሬን አዲስ የሆነ ችግር እንደገጠማት በግልጽ አምናለች።
አሁን ላይ ጦሩ የመከላከያ ሚኒስትሩን ወክለው በሚሰሩ ሚኒስትር እየተመራ ሲሆን ችግሩ መፍትሄ አላገኘም።