ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሁለት የአሜሪካ 'ፉትቦል' ተጫዋች በዘረፋ ወንጀል ተከሰሱ
የፍሎሪዳ ፖሊስ ሁለት ኤንኤፍኤል [የአሜሪካ 'ፉትቦል' ሊግ] ተጫዋቾችን በእግር በፈረስ እያፈላለገ ነው።
ዲአንደሬ ቤከር የተባለው የኒው ዮርክ ጃይንትስ ተጫዋችና ክዊንተን ዳንባር የተባለው የሲያትል ሲሃውክስ ተጫዋች በመሣሪያ በመታገዝ የዝርፊያ ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ተጠርጥረው ነው በፖሊስ እየተፈለጉ ያሉት።
ፖለስ እንደሚለው ተጫዎቾቹ 12 ሺህ ዶላርና 25 ሺህ ዶላር የሚያወጣ የእጅ ሰዓት ዘርፈዋል ሲል ይጠረጥራቸዋል።
ሁለቱም ግለሰቦች እስካሁን በቁጥጥር ሥር አልዋሉም። ፖሊስ ክስተቱን በተመለከተ ከሊጉ ኃላፊዎችና ከአንዱ ተጫዋች ጠበቃ ጋር መነጋገሩን አሳውቋል።
አልፎም ፖሊስ ሁለቱ ተጨዋቾች ራሳቸውን አሳልፈው ይሰጣሉ ብሎ እንደሚጠብቅ አሳውቋል።
እንደ ፖሊስ ዘገባ ከሆነ ተጫዋቾቹ ዝርፊያውን የፈፀሙት በአንድ የቤት ውስጥ ፓርቲ ላይ በተፈጠረ አለመግባባት ነው። ተዘረፉ የተባሉት ግለሰቦች የቪድዮ ጌምና ካርታ እየተጫወቱ እንደነበር ፖሊስ አክሎ አስታውቋል።
ከዚያም ቤከር የተሰኘው ግለሰብ ሽጉጥ በማውጣት ሲደግን ዳንባር እና አንድ ሌላ የፊት ጭምብሎ አድርጎ ነበር የተባለው ሰው ውድ ዋጋ ያላቸውን ንብረቶች ዘርፈዋል፤ ቀጥሎም ሦስቱ ግለሰቦች ለየብቻ መኪናቸውን አስነስተው ሄደዋል ይላል የፖሊስ መዝገብ።
የፊት ጭምብል አድርጎ ነበር የተባለው ግለሰብ ማንነቱ ሙሉ በሙሉ ይፋ አልሆነም።
ወንጀሉ ተፈፀመብን ከሚሉ ሰዎች መካከል አንዱ ወንጀሉ የታቀደበት ነው ሲል ቃሉን ለፖሊስ መስጠቱ ተነግሯል። ለዚህም ደግሞ እንደማስረጃ ያቀረበው ሦስቱም ግለሰቦች በየግል መኪናቸው ወደየፊናቸው መሄዳቸው ነው።
የ22 ዓመቱ ቤከር በስምንት ወንጀሎች እየተፈለገ ነው። የ27 ዓመቱ ዳንባር ደግሞ በአራት ወንጀሎች በፖሊስ ይፈለጋል።
የአሜሪካ ፉትቦል ሊግ [ኤንኤፍኤል] ስለ ክስተቱ እናውቃለን ነገር ግን ለጊዜው አስተያየት አንሰጥም ብሏል።
ሁለቱም ተጫዎቾች ለየክለባቸው የኋላ ተከላካይ መስመር ላይ ነው የሚሰለፉት።